Utility Manager's Message

እንደሚታወቀው በአስተዳደራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገቱ እየጨመረ የመጣውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ እድገትና ልማት፤ እንዲሁም በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የከተማ ህዝብ ቁጥር ታሳቢ ባደረገ መልኩ የውሃ አቅርቦቱን ከፍላጎት ጋር ለማጣጣም ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡

ያለፉ ጥረቶች እና ተግዳሮቶች

በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለውን ከፍተኛ ክፍተት ለመሙላት በአስተዳደሩና በውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር በጋራ በመሆን በ2005 እ.ኢ.አ አጋማሽ ላይ ከአለም ባንክ በተገኘ እርዳታ እና ብድር እንዲሁም በከተማው አስተዳደር አጣማሪ በጀት የመጀመሪያውን የድሬዳዋ ከተማ የመጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን ፕሮጀክት በመተግበር በሚያዝያ 2011 ዓ.ም ተጠናቆ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ለማሳካት ታቅዶ የነበረው ስራ በከተማው ዳርቻ መልካ ጀብዱ አካባቢ ሊሰራ የነበረው በበጀት እጥረት ምክንያት ባለ መተግበሩና በፕሮጀክቱ የተቆፈሩና ወደ ስራ የገቡ ጉድጓዶችም ቢሆን የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በመጣው የአካባቢ ሙቀት መጨመር ምክንያት ውሃ የመስጠት አቅማቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ እየቀነሰ በመምጣቱ እንዲሁም የድሬደዋ መጠጥ ውሃ ዋንኛ ችግር በሆነው ካልሽየም ባይካርቦኔት /በተለምዶ ጨው/ በሚባለው ንጥረ ነገር ምክንያት በተፈለገውና በታቀደው ልክ ተቋማችን ለከተማው ህብረተሰብ ውሃ በአመረተው ልክ ማቅረብ አልተቻለም፡፡

የተፈጠረውን ክፍተት ለማቃለል በውሃና ኢነርጂ ሚንስትር እና በአስተዳደሩ ድጋፍ ተጨማሪ ጉድጓዶች በመቆፈር ወደ አገልግሎት እንዲገባ ተደርጓል፡፡በተጨማሪም በበጀት እጥረት ምክንያት ከተጠናቀቀው ፕሮጀክት ተቆርጦ የቀረውና ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጀውን የመልካ ጀብዱ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ምዕራፍ አንድ በአስተዳደሩ አቅም ለማጠናቀቅ ባለፉት ሦስት አመታት ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በእስካሁኑ እንቅስቃሴም ከአስር ጉድጓዶች በላይ ቁፋሮ የማጠናቀቅ ስራ፣የተለያዩ የቧንቧና መገጣጠምያ ግዢ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን ቀሪ የፕሮጀክቱ ስራዎችንም በማፋጠን በ2017 ዓ.ም ወደ አገልግሎት ለመስገባት እየተሰራ ይገኛል፡፡

የረጅም ጊዜ የውሃ ዋስትና

ባለስልጣኑ በተለይም በውሀ አቅርቦት የሥራ ዘርፍ ረገድ የከተማችንን ዘለቄታዊ የውሀ ፍላጎት ማሟሏትን ታሳቢ ያደረጉ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር የውሀ መገኛ አማራጮችን ያካተቱ፣የ30 ዓመት የውሃ ፍላጎት ጥናት በማስጠናት ላይ የምንገኝ ሲሆን የካልሽየም ባይካርቦኔትን ችግር በዘለቄታው ለመቅረፍ የሚያስችል ጥናትንም በማስጠናት ችገሩን ለመፍታት የሚያስችል ከጥናት የተገኘ ሙሉ መረጃ በእጃችን ያለ ቢሆንም ፕሮጀክቱን ለመተግበር የሚያስችል የገንዘብ መጠን ከተቋማችንና ከአስተዳደሩም አቅም በላይ ስለሆነ በዘርፉ ያሉ አጋሮችን ድጋፍ ለማግኘት ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡

የንፅህና አጠባበቅ እና የቆሻሻ ውሃ አያያዝ

በሌላ በኩል ከውሃና ኢነርጂ ሚንስትር ጋር በመሆን ከአለም ባንክ በተገኘ የበጀት ድጋፍና ብድር ሁለተኛውን የውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ከ2013 ዓ/ም ጀምሮ በመጀመሪያው ዙር የትግበራ ምዕራፍ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገድ ዘርፉን ለማሻሻልና ለማዘመን የተጠና ጥናትን መሰረት ያደረጉ ጥረቶች በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ በአስካሁኑም እንቅስቃሴ

  • በከተማው ለሚገኙ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች 35 የጋራ መፀዳጃቤቶች፣ 11 የህዝብ መፀዳጃ ቤቶችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ማስረከብ የተቻለ ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎንም በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ለሆኑ ነዋሪዎችም የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ 1500 ለሚሆኑ የከተማው ነዋሪዎች አዲስ የውሃ መስመር እንዲገባላቸው ተደርጓል፡፡

  • ከዚሁ ጎን ለጎንም በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ለሆኑ ነዋሪዎችም የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ 1500 ለሚሆኑ የከተማው ነዋሪዎች አዲስ የውሃ መስመር እንዲገባላቸው ተደርጓል፡፡

  • በተያዘው በጀት ዓመትም (በ2015) 50 የጋራ መፀዳጃ እና 8 የህዝብ መፀዳጃ ቤቶችን በማስገንባት ላይ እንገኛለን፡፡

  • በተጨማሪም ለ8 የሕዝብና የጋራ መጸዳጃ ቤቶች በአገልግሎት ብዛት አገልግሎት መስጠት ያቆሙትንም እድሳት ለማድረግ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡

ለአገልግሎት መሻሻል ቁርጠኝነት

ተቋማችን በውሃ አቅርቦትና እና ስርጭት ብሎም የፍሳሽ አወጋገድ ስርአትን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለማዘመን ከመንግስትና ከህዝብ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣትና በትኩረት ለመስራት እንደምንተጋ እየገለጽኩኝ የከተማውም ህብረተሰብ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለስራችን ስኬት ከጎናችን እንዲሆን በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

በዚህ መጽሄት ላይ ለህበረተሰቡ የተቋሙን ዋና ዋና መረጃ ለማድረስ ጥረት የተደረገ ስለሆነ በመረጃዎቹ ተጠቃሚ እንደምትሆኑ እተማመናለሁ፡፡

“ውሃን በቁጠባ እንጠቀም”

አመሰግናለሁ

Amharic
Scroll to Top